Grace Reformed Baptist Church

በጸሎት ወደ እግዚአብሔር እናገራለሁ፤ በቃሉ ደግሞ የእርሱን ድምፅ እሰማለሁ

አብዛኞቻችን ካደግንበት ሁኔታ አንጻር አንዳንድ ልምምዶች በቀላሉ አይለቁንም። ያደግንበት አካባቢ በቀጥታ “Charismatic” ባይሆንም እንኳ፣ አዕምሮአችን የተቀረጸውና የተገነባው በዚያው አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል። ይህ ሁኔታ በብዙ መንገድ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ጎድቶታል ብዬ አስባለሁ።

በጸሎት ሕይወታችን ውስጥ ከሚገጥሙን ተግዳሮቶች አንዱ ነው ብዬ የማስበው “እግዚአብሔር እንደሰማኝ በምን አውቃለሁ?” የሚለው ጥያቄና ስጋት ነው። ለምንድነው እንዲህ የሚሰማን? መጽሐፍ ቅዱስስ ከጸሎት በኋላ ምን እንድንጠብቅ ይነግረናል? የሚሉ ጥያቄዎች በውስጣችን ለምን ይፈጠራሉ? በጸሎት መሰማታችንንስ የምናውቅበት የተለየ መንገድ አለ ወይ?

መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ቀጥተኛ የሆነ መልስ አለው። እርሱም በዮሐንስ መልዕክት ላይ እንዲህ ይነበባል፦

“14 በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። 15 የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን።” (1 ዮሐ 5)

ይህ የሚያሳየን ጸሎት የእምነት ጉዳይ መሆኑን ነው። ተከትሎት ሊሰማ የሚገባ የተለየ ስሜት የለም። እንደ ፈቃዱ የጸለየነውን ሁሉ እግዚአብሔር ይሰማል፤ እኛም እንደ ሰማን መቁጠር አለብን። እግዚአብሔር ጸሎቴን መመለሱን የሚነግረኝ በጆሮዬ በሹክሹክታ “ሰምቼሃለሁ” በማለት ሳይሆን፣ ቀጥሎ ባለው ሕይወቴ የለመንኩትን በመስጠት፣ ወይም ደግሞ “ባለመስጠት” (ይህም ራሱ መልስ ነው) ነው። ካልሆነም በመግቦቱ (Providence) ነገሩ የተለየ ዓላማ እንደነበረው ያሳየናል። ይህ እስከሚሆን ድረስ ግን፣ ልመናችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እስከሆነ ድረስ መጸለይን ማቆም የለብንም። እግዚአብሔር መልስ እስከሚሰጥ ወይም በመግቦቱ በሕይወታችን ውስጥ ያ ነገር ያለውን መንፈሳዊ ትርጉም እስከሚያሳየን ድረስ በጸሎት መጽናት አለብን።

በተሃድሶ ሥነ-መለኮት (Reformed Theology) ትምህርት፣ ጸሎት ከጸጋ መንገዶች (Means of Grace) መካከል አንዱ ነው። በካቴኪዝም (Catechism) ውስጥ የተቀመጠበት ቅደም ተከተል በዘፈቀደ ሳይሆን የራሱ የሆነ ሥነ-መለኮታዊ አንድምታ አለው። ለምሳሌ የሮሜ ወይም የኤፌሶን መጽሐፍት በጥንቃቄ በሥርዓት (Systematically) እንደተቀመጡ እንገነዛባለን። የተቀመጡበት ስርዓትም ስነ መለኮታዊ ትርጉም አለው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 1-3 ስለ ሰው ልጅ ውድቀትና አስከፊ የኃጢአት ሁኔታ እንጂ ድነት እንዴት እንደሚገኝ አያወራም። ስለ ክርስቶስ ማዳን ማውራት የሚጀምረው በምዕራፍ 3 አጋማሽ ላይ ነው። የዚህ አደራደር መልእክት ግልጽ ነው፦ “ሰው ያለበትን የኃጢአተኝነት ክፋት ካልተረዳ፣ የወንጌሉን የምሥራች በእውነተኛ ትርጉሙ ሊረዳ አይችልም።”

ወደ ጸሎት ሃሳባችን ስንመለስ ይህ መርህ በሉተር “ትንሹ ካቴኪዝም” ውስጥም ይንጸባረቃል። አደራደሩ፦

  1. ሕጉ (አሥርቱ ትእዛዛት)

  2. ወንጌል (የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ)

  3. ጸሎት (አባታችን ሆይ)

በሚል የተቀመጠ ነው። በሕጉና በወንጌሉ በኩል እግዚአብሔር ወደ እኛ ይመጣል፤ እኛ ደግሞ በኃጢአት ንስሐና በወንጌል እምነት ተስፋ ወደ እግዚአብሔር በተከፈተልን በር በጸሎት ወደ እርሱ እንሄዳለን። ይህ መርህ ወሳኝ ነው፤ በሕጉና በወንጌሉ በኩል የእግዚአብሔርን ፈቃድ አውቄ እጸልያለሁ።

ጸልዬ ስጨርስ መልሱን በሁለት መንገድ እጠብቃለሁ፦

  • በቃሉ ብርሃን፦ የሕይወቴን መንገድ እመረምራለሁ።

  • በመግቦቱ (Providence)፦ በሕይወቴ የሚከናወኑትን ነገሮች ከቃሉ ሥር ሆኜ እመለከታለሁ።

የእግዚአብሔርን ድምጽ ለመስማት የምጠብቀው በቃል ንባብና በስብከት ብቻ ነው። ካልሆነም ያነበብኩትን ቃል መንፈስ ቅዱስ በማንኛውም ጊዜ ወደ አዕምሮዬ አምጥቶ በትክክል እንዲገባኝ ሲያደርግ ፈቃዱን እረዳለሁ። በአጭሩ፤ ጸሎት እኔ ልመናዬን ወደ እግዚአብሔር የማቀርብበት “የማወራበት” ክፍል ሲሆን፣ በቅዱስ ቃሉ ደግሞ “ለመስማት” እቀመጣለሁ። ከዚያ ውጪ ድምፅ ፍለጋ በተሰወሩ መንገዶች አልሄድም።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEN
Scroll to Top